አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ሐምሌ ፳ ቀን ፳ ፻ ፩ ዓመተ ምህረት ( 7/27/2018 )
ትናንት አርብ፣ ሐምሌ ፳ ቀን ፳ ፻ ፩ ዓመተ ምህረት ( 7/27/2018 ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከተቃዋሚ/ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉትን ልውውጥ ከድረገጽ ካገኘሁት ቪዲዮ ላይ ተመለከትኩ። ዛሬም በዋሺንግተን ዲ. ሲ. ስብሰባ ያደርጋሉ። ከትናንቱ የተለየ እንደማይናገሩ እገምታለሁ። በአርቡ ስብሰባ፤ ከትንንሽ ድርጅቶች እስከ ትልልቅ ድርጅቶች፣ በዛ ካሉ የብሔር ድርጅቶች እስከ ሀገር አቀፍ ድርጅቶች፣ ከነባር ታጋይ ደርጅት መሪዎች እስከ ነባሮችን ጠይ ድርጅት መሪዋች ድረስ፤ አድናቆት ተቸራቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አውቶቡስ፤ ተሳፋሪዎችን ግራና ቀኝ ሲጠራና ሲያሳፍር ተመለከትኩ። አውቶቡሱ ደምቋል። የአረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ውስጡን ሞልቶታል። ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው ቅኝት አጥኖታል። ባሁኑ ስዓት ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና በስተቀር፤ አንዲትም ነጥብ በተቃራኒ ማንሳቱ፤ የትየለሌ ጠላትነት ነው። ይህ አንድም ሰማይ! አለያ መሬት! የሚል ሂደት፤ ትክክል እንዳልሆነ እሳቸው ገልጸውታል። እናም እንኳን መንግሥትና ሕዝቡ የምንሰማማበት ወቅት ላይ ደረስን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ፤ ብዙዎችን የሚያስደስቱ መልሶች ሠጡ። እኔም ባመዛኙ በመልሶቹ ረካሁ። ከመካከል ግን የቅርብ ታሪካችንን ዞሬ እንድመረምር ያደረጉኝ መልሶችን አገኘሁባቸው። ምንድን ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ በጣም ልብ የሚነካ ቅንነትና ሕዝባዊ ፍቅር አላቸው። የፖለቲካ ግንዛቤያቸውም ካሁን በፊት በመሪዎቻችን ያልታየ ነው። በግለሰብ ደረጃ መደነቅ ያለባቸው ናቸው። ሁላችን መርሳት የሌለብን ደግሞ፤ እሳቸው አንድ ግለሰብ ናቸው። የፖለቲካ ተመክሯቸው ደግሞ፤ አሁን ሊያፈርሱት እርዱኝ! እያሉ ካለው የኢሕአዴግ ሥርዓት የተሸመተ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ፤ የሀገራችን ችግር በጣም ጥልቅና ውስብስብ ስለሆነ፤ ጊዜ ወሳጅ ነው። እሳቸውም ይሄንኑ አስምረውበታል። በፖለቲካ ሂደት ደግሞ፤ ቋሚ የሆነ ባህርይ የለም። አሰላለፍ በየጊዜው ይቀያየራል። ፊት ለፊት ላጋጠመው የኅብረተሰብ ሁኔታ፤ መፍትሔ የሚሉትን ማቀንቀን የፖለቲካ ሂደት ማሽከርከሪያ ምሰሶው ነው። ዛሬ ጥሩ ያልነው ነገር፤ በቅጽበት ዋጋ ሊያጣ ይችላል። ምን ጊዜም ቋሚ ሆነው የሚቀጥሉት፤ ሕዝቡና ሀገሪቱ ናቸው። አምባገነን መሪዎች በመልክም ሆነ በቅርጽ ከኔና ከርስዎ የተለዩ አይደሉም። ቀንድ የላቸውም። የተለዩ ያገጠጡ ጥርሶችም የሏቸው። ሲጀምሩም፤ “አምባገነን ነኝ!” እያሉ በማወጅ አይደለም። ይሄንን ለማስረገጥ፤ ሩቅ ሳንሄድ፤ የራሳችንን የቅርብ ታሪክ ዞሮ መመልከቱ ይረዳል።
በ ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር አደባባይ ወጥቶ፤ የነበረውን መንግሥት “ወጊድልኝ!” ሲል፤ ተደራጅቶና ታጥቆ የነበረው ወታደራዊው ቡድን፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” “እናንተ በያላችሁበት አርፋችሁ ተቀመጡ! እኔ ሁሉን አደርገዋለሁ!” በማለት መድረኩን ለብቻው ተቆጣጠረ። አስታውሳለሁ፤ አንድ ወዳጄ፤ “እስኪ ተዋቸው! ጥሩ ይዘዋል! አሁን እኛ፤ በየሙያ መስካችን ጠንክረን መሥራት ብቻ ነው ያለብን! እነሱ አንድ በአንድ እያሉ፤ ልክ ያስገቡታል!” ብሎ ተከራከረኝ። እውነትም ሁሉንም ልክ አስገቡት! መሬት!!! ደርጋማው ወታደራዊ መንግሥት፤ ላንድ ሰሞን ጋዜጣዎችን ነፃ አደረገ፡ ውይይት ፈቀድኩ አለና ሰውን አንጫጫ። ከዚያ ለቃቅሞ መሬት አገባቸው። ሰው በላውን መንግሥቱ ኃይለማርያም ለዘለዓለም አንግሦ፤ እኔው ነኝ ሽግግር መንግሥት አለና፤ በበነጋታው እኔው ነኝ መንግሥት ብሎን ቁጭ አለ።
በተመሳሳይ መልኩ፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ሲገባ፤ ብሔሮች ነፃ ወጡ አለን። ከሰው በላው መንግሥቱ ኃይለማርያም አዳንኳችሁ አለን። በደርግ ጊዜ የጠፉት ነፍጠኞች፣ ትምክህተኞችና ፊውዳሎች ነፍስ ዘርተው መጥተው፣ ዓይን አፍጥጠው ተገትረው፣ ክንፋቸውን ዘርግተው ሕዝቡን ካሰሩበት ማነቆ፤ ነፃ አውጣኋችሁ ተባልን። ዴሞክራሲ ነገሰ ተባልን። ኢትዮጵያ ያልነበራት ሕገ መንግሥት አገኘች ተባልን። አዲስ ታሪክ ተጻፈልን። ከዐማራና ለተዋሕዶ በኢተክርስትያን ተላቀቃችሁ ተባልን። ወደፊት ልናይ ነው ተብለን፤ ፊታችንን ወደፊት ስናዞር፤ አንኳንስ ዴሞክራሲ ሰፍኖ አዳዲስ ፓርቲዎች ሊፋፉ፤ አብረው ተማክረው የገቡት የትግራይ፣ የኦሮሞና የኤርትራ ነፃ አውጪዎቹም ተለያይተው ተጨራረሱ። የራሳቸው የሚባል ትውልድ ሰለሌላቸው፤ ያው የፈረደብንን ኢትዮጵያዊያንን በነሱው ጦርነት ማገዱን። ብዙዎች አለቁ። ከዚያማ ሀገራችን እንኳንስ ለውጪዎቹ፤ በውስጥ ላሉት ኢትዮጵያዊያን አዲስ እስከትሆን ድረስ ሁለንተናዋ የተለዋወጠ ኢትዮጵያ ተከሰተች። ባህል፤ ወግ፣ ስነ ሥርዓት፣ ታሪክ፣ በሕዝብ መካከል የነበረው መተሳሰብ ቦታ ተነፈገ።
አሁን፤ በሕዝቡ፤ በተለይም በወጣቱ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት፤ ለዚህ በቅተናል። ታዲያ ከዚህ ወደፊት ለመሄድ ሲታሰብ፤ የት ነበርን? እንዴት ለዚህ በቃን? ወደፊት ለመሄድ አሁን በቦታው ምን አለን? የሚለውን መመልከቱ የግድ ነው። ዝርዝር መግባቱ ቀባሪውን ማርዳት ነው። በቀጥታ ወደ ተነሳሁበት እመለሳለሁ። የመጀመሪያው ለሽግግር መንግሥት ጥያቄ የሠጡትን መልስ በሚመለከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለዐማራው የሕልውና ጉዳይ የሠጡት ትኩረት ወይንም የትኩረት ማነስ ነው። በየተራ ልሂድባቸው።
የሽግግር ጥያቄ ለምን ተነሳ? ምን ማለትስ ነው?
የሽግግር መንግሥት፤ ከነበረው ወደምንፈልገው ለመሄድ መሸጋገሪያ ድልድዩ ነው። ዛሬ የምንፈልገውን ለማግኘት፤ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ፤ የተወሳሰበና ቀና ባለመሆኑ፤ ያንን ለመደልደል እና ለማዘጋጀት፤ የግድ መንገዱን ለማለሳለስ፤ ሁሉም የሀገሪቱ ተቆርቋሪዎች የሚሳተፍበት ቡድን ማዘጋጀት የግድ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው፤ የኢሕአዴግ ፓርቲ ነው። ኢሕአዴግ ራሱን እያሻሸለ ለመሆኑ መስካሪ የሚፈልግ የለም። እያየነው ነው። አሁንም ሀገራችን የአንድ ፓርቲ ሀገር ናት። ምንም ይሁን ምንም፤ ሀገራችን የአንድ ፓርቲ ሀገር ሆና፤ ነገ የብዙ ፓርቲዎች ሀገር ትሆናለች በሚል ተስፋ ወደፊት መሄድ ያዳግታል። ዛሬውኑ ዘለን የብዙ ፓርቲዎች ሀገር ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ከአንድ ፓርቲ ወደ ብዙ ፓርቲዎች ለመሸጋገር፤ የግድ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል። ያ ነው የሽግግር መንግሥት ጥያቄው መሠረቱ። ያንን ዘሎ ማለፍ አይቻልም። ቆዩኝ እኔ አደርገዋለሁ የሚለው ንግግር፣ መንግሥቱ ኃይለማርያምን፣ መለስ ዜናውን ያስታውሱኛል። ያን መስማት ይዘገንናል። የነገዋን ትክክለኛ መንገድ የያዘች ሀገራችን እንድትሆን፤ የግድ የሽግግር ጊዜ ያስፈልገናል። በርግጥ የሽግግሩ መንግሥት አመሠራረትና ይዘት በትክክል መያዝ አለበት። ሆኖም ግን፤ አደጋ አለው! እና ወይንም ሁሉም መንግሥት የሽግግር መንግሥት ነው! የሚለው አያስኬድም። Wንነት ከዚህ ይጀምራል።
የዐማራውን ጥያቄ በሚመለከት፤
ዐማራው እንደሌላው የሀገራችን ሕዝብ ከፍተኛ በደል ተካሂዶበታል። እዚህ ላይ ጥያቄ የለም። የዐማራውን በደል፤ ከጥፋቱ ልክ የለሽነት በላይ፤ ልዩ የሚያደርጉት ግልጽ የሆኑ ኩኔቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፤ ዐማራው በተናጠል፤ “እስከዛሬ በዳይ ሕዝብ ነበር!” በሚል ተፈርጆ ነበር። የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ገና ሲመሠረት፤ “በዐማራው መቃብር ላይ የትግራይ ሩፑብሊክን እመሠርታለሁ!” ብሎ ነበር የተነሳው። በተግባርም ዐማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያላደረገው ነገር የለም። ቀጥሎም ያቋቋማቸው ተቀጥላ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ፤ ብዐዴንን ጨምሮ፤ ይሄን መተከል የኔ ብለው፤ ዐማራን የዘር ማጽዳት ፈጽመውበታል። ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ፤ በመላ ኢትዮጵያ ለምዕተ ዐመታት ኖሯል። ዐማራው ከመላ ኢትዮጵያ እየተፈናቀለ፤ እየተዘረፈ፣ እየተገደለ፣ እየተሰደደ ነበር። ይህ የተለየ በደል፤ አሁንም በግልጽ በራሱ መኖሪያ በሆኑት፤ በወልቃይት፤ በራያ፣ በጠለምት፤ “ትግሬ ነኝ ብለህ ኑር! ወይንም ከዚህ ጥፋ!” ተብሎ ተወጥሯል። መተከል፤ “ያንተ ቦታ አይደለም!” ተብሎ፤ የደረሰበትን በጽሑፍ ማስቀመጡ ይዘገንናል። በዚህ ሁኔታ፤ ሀቁ የሚነግረን ይሄ ሆኖ ሳለ፤ “ሁሉም እኩል ነው!” ብሎ አጨብጭቡና ተደመሩ ብቻ ማለቱ ለኔ አያስኬድም።
ለዐማራው፤ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የተለዬ፤ ልዩ የሆነ ሥጦታ ይለገሰው የሚል የለም። ነገር ግን፤ ዐማራው አሁንም የሕልውና ጥያቄ አለው። አሁንም በአደጋ ላይ ነው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና መንግሥታቸው ሊያደርጉ የሚችሉት የተወሰነ ነው። አብላጫው ድርሻ፤ ዐማራው ራሱ ሊያደርገው የሚገባው ነው። በወልቃይት፣ በጠለምት፣ በራያ፣ በመተከል የሚኖረው ዐማራ አሁንም በእስር ቤት ውስጥ ነው። የተፈናቀሉ ዐማራዎች አሁንም በየመንገዱ ተጥለው ነው የሚገኙት። ሌላው በሂደት የሚተገበር ይሆናል። ዋናው ግን፤ ይሄን የዐማራውን የሕልውና አደጋ መገንዘብ ነው።
ይሄን ሁሉ ካሰፈርኩ በኋላ፤ አሁንም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ያለኝን አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ። ሁላችንም እስከዛሬ ይሆናል ብለን ያልገመትነው ገሃድ ሆኖ ስናየው፤ በደስታ መጥለቅለቃችን ያለ ነው። ፊታችንን ስንመለከት፤ ጀርባችንን መዳሰስና የነበርንበትን መፈተሹ፤ ትምህርት ይሠጠናል። ወደን የሰቀልነውን ብቅል፤ ኋላ ማውረዱ እንዳይከብደን፤ ካሁኑ አሰቃቀላችንን እንወቅበት። አመሰግናለሁ። eske.meche@yahoo.com

















