በሀገራችን ላይ የተቃጣውን ባህላዊ ዘረፋ እንታደግ

ሥናፍቅሽ ግርማ

ሀገራት ለኤኮኖሚ ድጋፋቸው ከሚጠቀሙበት ስልቶች አንዱና ዋናኛው ያላቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብት መንከባከብ፣ መጠበቅና በተቻለ መጠንም ማሳደግ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሀገራቸን ኢትዮጵያ ያሏትን በተጠቀሱት ዘርፍ የሚገኙትን ሀብቷን በአግባቡ ከተጠቀመች የኤኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግና በዚህም የሕዝቧን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደምትችል አያጠያይቅም፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የስራ ዘርፍ በመትጋት ሀገራዊና ወገናዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የበቃን ሆነን መገኘት አለብን፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያበረከተቻቸው እፁብ ድንቅ የሆኑ ክንውኖች ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ በሆነውና ‹ጢስ አልባ› ተብሎ በሚታወቀው የቱሪዝም ክፍለ ኤኮኖሚ ሀገራችን ከምትታወቅባቸው መስህቦች መካከል – በጎንደር የሚገኘው የፋሲለደስ ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የኦሞ ሸለቆ፣ የባሌና የሰሜን ተራሮች፣ የዳንከል ዝቅተኛ ቦታዎች፣ የተለያዩ የዱር እንስሳት (በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ዋልያ የመሳሰሉ እንዳሉ ያጤኗል)፣ ልዮ ልዮ የእዋፋት ዝርያዎች. . . ወዘተ በዚሁ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ከላይ የተገለጹት ለቱሪዝም እድገት ድርሻቸው ከፍተኛ የሆኑ መስህቦች ቢሆኑም ሀገሪቱ በዚሁ ክፍለ ኤኬኖሚ ያገኘችው ጥቅም አነስተኛ ነው፡፡ በተለይ ከሌሎች አጎራባች ከሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ሲወዳደር ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብት አንጻር በዚሁ የሙያ ዘርፍ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነች አሃዞች ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ እኤአ በ2015 ግብጽን 9.1 ሚልዮን፣ ኬንያን 1.3 ሚልዮን ቱሪስቶች ጎብኝታዋል፡፡ በዚህኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶች 871ሺ ነበሩ፡፡ ከዚህ በላይ ከኢትዮጵያ ጋር በማወዳደር ያቀረብኳቸው ሀገራትን ለማቅረብ የተገደድኩት ካላቸው የቱሪስት መስህብ አንጻር ከእኛይቱ ኢትዮጵያ ጋር የሚወዳደሩ ሆነው ያለመገኘታቸው ነው፡፡ የኬንያን ስንመለከት ዋናው የዱር እንስሳትና ይህንኑ በብቃት ለማስጎብኘት ያዘጋጀቻቸው ፓርኮች ሲሆኑ፣ በግብፅ በኩል ደግሞ ጥንታዊ ሐውልቶችና ታሪካዊ ግንቦች እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ይህም እንደ ፒራሜድና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህንን ማንሳት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ እነዚህ የተጠቀሱት የሁለቱ ሀገራት የቱሪስት መስህቦች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ያላት መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ሀቅ መሆኑን ለመጥቀስ ነው፡፡

ልንጠብቃቸውና ልንከባከባቸው የሚገበ ዕሴትና ንብረቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ አየተሸረሸሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም መሸርሸር ምክንያት ከተጠቃሾቹ ዋንኛው እኛው ኢትዮጵያዊያን ሆነን እንገኛለን፡፡ ይህንኑ በአጭር ምሳሌ ለማስረዳት – በዓለም አቀፍ ደረጃ ለውድድር በተለያዩ ሀገራት የሚሄዲ አትሌቶቻችን ለብሰው የሚሄዱት ቱታም ሆነ ሌላ ልብስ ላይ ስማቸውና ሀገራቸው ይጻፋል፡፡ እንኳን በአትሌት ደረጃ በማናቸው ምክንያት ከሀገሩ የሚወጣ ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር እንደሆነ ሊሰማው ይገባል፡፡ እንዚህ አትሌቶች በጀርባቸውና በደረታቸው የሚጻፈው በሀገርኛ ፊደል ቢሆንና ሌላው ማለትም እንግሊዝኛው ቢከተል ሀገርን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአፍሪካ ብቸኛው ፊደል ያለታ ሀገር የእኛይቱ ኢትዮጵያ እንደሆነች አንርሳ፡፡ አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ኦሮሚኛ፣ የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት ሆነን አብዛኛዎች አትሌቶች በተለያዩ መድርኮች በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢናገሩ ያለብዙ ችግር ሀሳባቸውን መግለጽ ሲችሉ የመልዐክት ቋንቋ ነው የተባሉ ይመስል በእንግሊዝኛ ሲኮላተፉ መስማት ያሳዝናል፡፡

በሌላ በኩል የእኛ የሆኑና የብቸኛነት ባለቤትነት ያሉንን አንጸባራቂ ንብረቶቻችንን በተለያየ መልኩ እየተሰረቁ ባለቤትነታችን ፈሩን እየለቀቀ ነው፡፡ ‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል› እንደሚባለው ይህንንም ዘረፋ አስመልክቶ በቅርቡ የተከሰቱትን በአጭሩ እንመልከት፡፡

ጤፍን በማምረት እንዲሁም በምርቱ በመጠቀም ብቸኛ ሕዝብ እንደሆንን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ዛሬ እንደምንሰማው ከባህር ማዶ የሚገኝ ሀገር የባለቤትነት መብቱ የእኔ ነው እያለ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ፍንትው አድርጎ በሚገልፅ መልኩ የሚሰሩት የሽመናና የጥልፍ ውጤቶች ውበታቸውና ድምቀታቸው ወደር የማይገኝላቸው ናቸው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው እነዚሁ የሽመናና የጥልፍ ውጤቶች እንዲሁም ለሌች ቅርፃ ቅርፆች  ናሙናቸው ወደ ቻይና እየተሸጋገረ የኛኑ አሰራር ከእነሱ ጋር እያደባለቁ ለሺያጭ (Export) እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ከሚላክላቸው ሀገራት እኛም እንገኝበታለን፡፡

እነዚህ ንብረቶቻችን እየተዘረፉ መሄድ ጉዳቱ በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከጉዳቶቹም መካከል ሊጠቀስ የሚገባው እነዚህኑ ምርቶች በብዙ ልፋት የሚሰሩት ወገኖቻችን ርካሽ በሆነ ወረራ የሚደርስባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው፡፡

ታሪካዊ እሴቶቻችን – በንብረት፣ በቋንቋ፣ በበህልና በመሳሰለው የሚደረግብንን ዘረፋ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ሊታገለው የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ አባቶቻችን፣ እናቶቻችንና አያቶቻችን አሁን የእኛ ነው ብለን የምንኮራበትን መለያዎቻችንን ለመስራትና ለማቆየት ብዙ መስዋዕትነትን እንደከፈሉ በማወቅ እኛም ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የበቃን ሆነን መገኘት እንዳለብን ልናምን ይገባል፡፡ ማመን ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተቻለውን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የተደረገውን ይህን ዘረፋና ወረራ መንግሥትም በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ እንዲገኝለት ዋንኛው አካል እንደመሆኑ ሳይታክት ሊሰራበት ይገባል፡፡

 

በመጠኑም ቢሆን በተነሳው በዚህ ርዕስ ላይ ‹ትራቭል ኢትዮጵያ› የተባለ ድርጅት በተመሳሳይ መልኩ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀረበውን አስተያየት በቅርቡ ከፌስቡክ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ይህን የመሰለው ዓብይ ሀገራዊ ጉዳይ መሥሪያቤቶቹ ትኩረት ሰጥተው አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉንና በመፍትሄውም በኩል ዛሬ ነገ ሳይሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ በአንክሮ አሳስባለሁ፡፡

Share: