የተቃዋሚ ድርጅቶችና የሚጠብቃቸው ፈተና!

ባይሳ ዋቅ-ወያ

ይህ መልክቴ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በማንኛውም መልኩ ተደራጅተው ለሚገኙ የፖሊቲካ ድርጅቶች ነው። መቼም የኛን ይሁንታ ሳታገኙ እንወክላችኋለን ብላችሁ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያሳሰባችሁን ስለሆነ፣ “መወከሌ” ካልቀረ ደግሞ የሚሰማኝን ለማካፈል ያህል ነው። የማንኛችሁም አባል ስላልሆንኩ ደፍሬ ለመናገር ችያለሁና በጥሞና አድምጡኝ።

ወደ ቁም ነገሩ ከመግባቴ በፊት ግን አንዳንድ ነባራዊ ዕውኔታዎችን ለማንሳት እሻለሁ። በመጀመርያ ደረጃ፣ ከላይም ለማለት እንደሞከርኩት፣ አንዳችሁም ከሕዝብ የተቀበላችሁት አደራ ወይም በምርጫ የተሰጣችሁ ውክልና የለም። ሁላችሁም ራሳችሁን የሾማችሁ፣ ግን ደግሞ ከማህበረሰቡ ቀድማችሁ በመንቃታችሁና የህዝባችንን በደል ተገንዝባችሁ አገሪቷን ወደተሻለ አስተዳደራዊ ሥርዓትና የህዝቡንም የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በማሰብ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላችሁ ጓደኞቻችሁ ጋር ሆናችሁ በሚስማማችሁ መንገድ የየራሳችሁን ድርጅት የፈጠራችሁ ናችሁ። በመሆኑም፣ የናንተ ድርሻ ሕዝቡ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ በሆነ የፖሊቲካ ምህዳር ውስጥ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንጂ፣ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያን ሕዛብ ወክላችሁ ስለወደፊቱ የኢትዮጵያና ብሎም የኢትዮጵያውያን ዕድል ለመወሰን አትችሉም። ያን የሚወስነው ሕዝቡ ራሱ ነው። ስለሆነም፣ የናንተ ድርሻ፣ የሚሰማችሁንና ላገሪቷ ይበጃል የምትሉትን ፖሊቲካዊ አስተዳደርና የኤኮኖሚ ፖሊሲ ለሕዝቡ አቅርቦ ማሳመን መቻል ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ “የተለያየ አስተሳሰብ” የምታስተናግዱ ወደ መቶ የምትጠጉ ድርጅቶች ቁጥራችሁ ብዙ ስለሆነ፣ ልዩነታችሁን አቻችላችሁ ተቀራርቦ ባንድ ጣራ ሥር ሆኖ “የተደመረ” ሃሳብን ለሕዝቡ አቅርቦ “መሸጥ” መቻል ይኖርባችኋል። በኔ ግምት፣ ይህ ልዩነትን አቻችሎ፣ በሚያቀራርብ አስተሳሰብ ላይ የጋራ አቋም ወስዶ የተለያዩ ድርጅቶችን ባንድ ማዕክል ሥር ማዋቀር መቻል በቀላሉ የማይደረስበትና በባህላችንም ያልተለመደ በመሆኑ፣ የሁላችሁም ራስ ምታት እንደሆነ እገምታለሁ። እግዜር ብቻ ይሁናችሁ!

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለውን የኤኮኖሚና ማህበራዊ ቀውሶችን በሚቀጥለው ምርጫ ተወዳድሮ የሚያሸንፈው አካል ወይም ቡድን እንዴት አድርጎ ችግሩን በመቅረፍ፣ አገራችንን ከገባችበት መቀመቅ አውጥቶአት ኩሩ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባል የምትሆንበትን፣ ዜጎቿ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡበት፣ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውና ዕድሜው ከሰላሳ አምስት ዓመት በታች የሆነው የዛሬው ትውልድ በሙያው ሰርቶና ተከብሮ የሚኖርበት እንጂ ሥራ በማጣት ምክንያት ካገር ተሰዶ የሰሃራ በረሃ ሙቀት፣ የአረብ ሽፍቶች ግፍ ወይም የቀይ ባህር ወጀብ ሰለባ የማይሆንበትና በኤኮኖሚ የዳበረች ሰላማዊ አገር ሊፈጥር ይችላል የሚለውን ለዓመታት በጭንቅላቴ ሲመላለስ የነበረውን አገራዊ ችግር ላካፍላችሁ  ነው። መፍትሔ ኖሮኝ ወይም ከናንተ ቅጽበታዊ መፍትሔ ጠብቄ ሳይሆን፣ ችግሩ ወቅታዊ እንደሆነ ለመጠቆምና “የምትወክሉን” የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ማለቂያ በሌለው የፖሊቲካ ጥያቄ ላይ ነጋም ጠባም ከምትናቆሩ፣ እንደው አንድ ቀን በለስ ቀንቷችሁ በምርጫ አሸንፋችሁ የፖሊቲካ ሥልጣኑን ብትረከቡ፣ እንዴት አድርጋችሁ እነዚህን ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ቀውሶችን ቀርፋችሁ ካንድ ምዕተ ዓመት በላይ ደጋግሞ ቢጠይቅም መልስ ሊያገኝ ላልቻለው ሕዝባችን መልሱን ልትሰጡ የምትችሉት በማለት ላንድ ጊዜ እንኳ ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ለመኮርኮር ያህል ነው።

ስለፖሊቲካ ሥልጣን ማውራትና እንዴት አሸናፊ መሆን እንደሚቻል በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር ደረጃ ማስቀመጥ በጣም ቀላል ነው። በኛ ዘመን፣ ግራ ዘመም አስተሳሰቦችን በማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብ ጠቅልለን፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚቻለው ወዛደራዊ አምባገነንነትን ማስፈን ነው ብለን በተቻለን ሁሉ በፊውዳሉ ሥርዓት ላይ ዘመትንበት። ጽንፈ ሃሳቡ ትክክል ይሁን አይሁን በደንብ ሳናጣጥም ወታደራዊ አስተዳደሩ ጣልቃ ገብቶ “በራሱ አካሄድ” ብሔራዊ ችግሩን ለመቅረፍ ሞከረ። ሳያድለን ቀርቶ፣ ሕዝባችን እንኳን ሊጠግብና በልቶም ሊያድር አልቻለም! የተጠበቀው ሰላምም አልሰፈነም። እሱን የተካው ኢህአዴግም ቢሆን “በራሱ መንገድ” ማለትም በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ያነበነበውን፣ ለብሔራዊ  ችግሩ መፍትሔ ነው ብሎ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ሲዳክር ቆይቶ፣ ይኼው ዛሬም  ድረስ ሕዝቡም በልቶ አላደረም፣ ከሰላምና ጥጋብም ጋር እንደተኮራረፍን ቀረን።

በሁለት ዓመት ውስጥ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚደረግ ከወድሁ እየተነገረን ነው። ታድያ በምርጫው ተወዳድረን እናሸንፋለን የምትሉ ፖሊቲካ ድርጅቶቻችን፣ እነዚህን ብሔራዊ ቀውሶችን እንዴት አድርጋችሁ እንደምትፈቱ በውል አስባችሁበት ይሆን የሚል ትልቅ ጥያቄ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። ሳያችሁ ሳያችሁ፣ ብዙዎቻችሁም ደጋግማችሁ የምታነሱት ስለ ፖሊቲካ ሥልጣን እንጂ ለቀውሶቹ መፍትሔ ስትሰነዝሩ ሰምቼ አላውቅም። የሁላችሁም ጥያቄ “ኢህአዴግ ተወግዶ በሕዝብ በተመረጠ አካል መተካት አለበት” ነው። በያገሩ በምታካሄዱት ስብሰባና ኮንፈረንስም ከዚሁ የፖሊቲካ ሥልጣን ጥያቄ ዙሪያ ርቆ የማይሄድና ግፋም ቢል ደግሞ “ከፌዴራሊዝም ወይም የክልል አስተዳደር መጥፎነት” “ከጎሣ ፖሊቲካ” ወይም “ባንዲራው ላይ ስላለው አርማ” እና ከመሳሰሉት ርቆ የማይሄድና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፖሊቲካ ሥልጣን ጋር በተያያዘ ጉዳይ እንጂ፣ ስላገሪቷ የኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ወይም ማኅበረ ሰባዊ ቀውስን ለመዳሰስ ስታወያዩን አልተስተዋለም።

በኔ ግምት፣ የችግሮቻችን ቅርጫት እንደለማኝ ኮረጆ ነው። ከፖሊቲካ ሥልጣን ባሻገር፣ የሥራ አጥነት፣ የሙስና፣ የረሃብና የእርዛት፣ የፍልሰትና የመፈናቀል፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እናም የመሳሰሉትን የተለያዩ ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን ባንድ ላይ አምቆ የያዘ ይመስለኛል። ባንድ ላይ ከመታመቃቸው የተነሳ አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማየት የሚቻልበት ሁኔታም ያለ አይመስለኝም። ያለው አማራጭ ሁሉንም ባንድ ላይ መዋጥ ወይም መጣል ነው። የማህበረሰብ ጉዳይ ደግሞ በሆነ መንገድ መፍትሔ መፈለግ ነው እንጂ አንድ ላይ ታምቆ እንደበሰበስ የልመና ምግብ መጣል ስለማይቻል፣ ከወድሁ መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው ባይ ነኝ።

የኤኮኖሚው ሁኔታ እጅግ በጣም ዘግናኝ ነው። “አገሪቷን ለማልማት” ተብሎ የተወሰደው ብድር ብዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ተበዳሪ አገሮች በመጀመርያ ተርታ እንዳሰለፈን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በብድር የተሰሩት ፎቆችና ትላልቅ ህንጻዎች “ከወገብ በላይ” ያሉትን ሊከራይ የሚችል መካከለኛ የማህበረሰቡ አካል (middle class) ባለመኖሩ በመዲናችንና በክልል ዋና ከተሞች የሚገኙ ፎቆች ያገር ሃብት መሆናቸው ቀርቶ ያገር ዕዳ እየሆኑ ነው። ህንጻዎችን ለመገንባት ወይም ለልማት ፕሮጄክቶች ተብለው የተሰጡ ብድሮች “ባለ ዕዳዎቹ ከስረዋል ተብለው”፣ አበዳሪው ባንክ ከስሮ ተበዳሪዎቹ ደግሞ ገንዘቡን ካገር ማሸሻቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ገበሬው በያመቱ ተገዶ ማዳበርያ እንዲበደር ይደረግና፣ ለዘመናት በማዳበርያ የደነዘዘው የርሻ መሬት አጥጋቢ ምርት ባይሰጥም፣ ከሚመረተው ሰብል ደግሞ ከመንግሥት ግብር ሁሉ አስቀድሞ የማዳበርያ ብድር መክፈል ስላለበት አርሶ አደሩ ቤተሰቡን መመገብ አቅቶት ለዓመታት ለረሃብ ተዳርጓል። በያመቱ ከዩኒቬርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶች ሊያስተናግዳቸው የሚችል የኤኮኖሚ ዘርፍ ስለሌለና ያለው ምርጫ ድንጋይ መፍለጥ፣ ዘበኝነት ወይም ተመሳሳይ የሆነ፣ ከተለፋበት የትምህርት ዘመንና ውጤት ጋር የማይመጥን ሥራ በመሆኑ፣ እህቶቻችን ማንነታቸውንና ስብዕናቸውን  ሽጠውና አዋርደው ወደ ዓረብ አገሮች ለግርድና ይሄዳሉ፣ ሌሎች ደግሞ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበሮችን አቆራርጠው፣ የተሻለ ሕይወት ይገኝ ይሆናል በሚል ተስፋ ውድ ሕይወታቸውን እየገበሩ ይገኛሉ። ለሩብ ምዕት ዓመት አገሪቷን ከዳር እስከዳር ያቀናጀ ሙስና፣ እንደ ድሮው ዘመን በተወሰነ የአገልግሎት መስጫና ፍትህ ተቋማት ብቻ ሳይወሰን፣ በአራቱም ማዕዘናት ባህል ሆኖ ሁሉንም እየዘረፈና እያንገፈገፈ ስለሆነ፣ እንኳን በዚህ ትውልድ ይቅርና በሚቀጥለውም ትውልድ መቀረፉ ያጠራጥራል። ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ፎቅ እንኳ የሚሰረቅበት አገር! ሌሎችንም ብዙ ብዙ ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል፣ ለማመላከት ያህል ግን የሚበቃን ስለመሰለኝ እዚሁ ላይ ላቁም።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ ችግሮቻችን ኢህአዴግ የፈጠራቸው አይደሉም። የሰፊው ሕዝብ የድህነት ኑሮ በምኒልክና ዘውዲቱ ጊዜ አናውቅም እንጂ፣ ከዓጼው ዘመን ጀምሮ ያለ ነው። ልዩነቱ ያኔ አንጻራዊ መረጋጋት ስላለና የተማረውም ዜጋ ቁጥር ብዙ ባላመሆኑ፣ ተምሮ ሥራ ማጣት የሚባል ነገር ስለሌለ በአጼው ዘመን ውጭ አገር የተማሩት እንኳ ሳይቀሩ ያላንዳች መዘግየት ወዳገር ቤት ተመልሰው ይሾማሉ። አገር ጥሎ የሚኮበልል ወጣትም አልነበረም።

ችግሮቻችንን ዘርፈ-ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹ ባጭር ጊዜና አነስተኛ ወጪ ሊቀረፉ የሚችሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜና ከባድ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። ለምሳሌ የዜጎች ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳይጣስ ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ብቻ በቂ ነው። ብዙ ወጪ አይጠይቅም። የክልሎችን አስተዳደርና የሕዝቡን ፍላጎት በረፌሬንደም ማቃለልም እንደዚሁ። በሥልጣን በሚባልጉት ላይ ተገቢ እርምጃ ወስዶ ለሕዝቡ ብሶት መድረስ ይቻላል። ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር በመስማማትና በዕርዳታ ድጎማ የእስር ቤቶችን ሁኔታ ማሻሻል ይቻላል፣ የፍትህና የፖሊስ እንዲሁም የመርማሪዎችን የማሰልጠኛ ተቋማት በዲሞኪራሲያዊ ባሕል ታንጸው ሕዝባዊ እንዲሆኑ ማስተማር ይችላል። የፖሊቲካ ሥልጣን ችግሩም እንደዚሁ በቀላሉ በአነስተና ወጪ ሊቀረፍ ይችላል። ያለምንም ጣልቃ ገብነትና ታዛቢዎች በተገኙበት በሚካሄደው ምርጫ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ወይም ቡድን፣ ሥልጣኑን ተረክቦ መንግሥት ሊመሰርት ይችላል። ይህም ቀላል ነገር ነው።

በእኔ ግምት እጅግ በጣም አሳሳቢውና ለመቅረፍም ረጅም ጊዜና ብዙ ወጪ የሚጠይቀው የኤኮኖሚው ጉዳይ ነው። ደርግ “የተረከብኩት ባዶ ካዚና ነው” ሲለን በደንብ አልገባንም ነበር። ዛሬም በየቀኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኩል እንደሚነገረን ከሆነ፣ የአገሪቷን ኤኮኖሚ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደ ግል ንብረታቸው ያሾሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦችና ድርጅቶች መሆናቸውንና የተሰረቀውም ሃብት የተከማቸው ባገሪቷ ባንክ ሳይሆን በውጭ አገር ባንኮችና በተለያዩ ሰዎች ስም ስለሆነ ክትትል እንኳ ቢደረግበት ለማስመለስ ያለው ዕድል በጣም የመነመነ በመሆኑ ያገሪቷ ኤኮኖሚ እንደ ደቀቀ ለብዙ ዓመታት የሚቀጥል ይመስለኛል። ዛሬም ካዚናው ባዶ ነው ማለቴ ነው። አርሶ አደሩ ሕዝብ የተራበና የታረዘ፣ ወጣቱ ደግሞ ሥራ ያጣና ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶት፣ የሚቀጥለው ምርጫ ፍትሓዊ ይሆንና የፖሊቲካ ሥልጣኑን የሚጨብጠው አካል ወይም ቡድን ለችግሬ መፍትሔ ያስገኝልኛል ብሎ በጉጉት የሚጠብቅ ነው። ቄሮ፣ ፋኖና ሌሎችም ባለፉት አራት ዓመታት የከፈሉት ውድ ዋጋ፣ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠብቆላቸው ባገራቸው ሰርተው በክብር ለመኖር እንጂ አራት ኪሎ ሄደው የፖሊቲካ ወንበር ላይ ለመቆናጠጥ ስላልነበር፣ ህወሃት – መራሹን ኢህአዴግን ካንበረከኩ በኋላ፣ የሚቀጥለው “ሕዝባዊ መንግሥት” ለጥያቄያችን መልስ ይሰጠናል ብለው በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

እነዚህን ችግሮች ያቀፈን ቅርጫት ነው እንግዲህ የሚቀጥለው አሸናፊ ፓርቲ ወይም ቡድን የሚወርሰው። የዚህን በጉጉት የሚጠብቀውን ሕዝብ ሕልምና ምኞትን ነው እንግዲህ የሚቀጥለው የአራት ኪሎ ተረኛ ባጭር ጊዜ ውስጥ መቅረፍ ያለበት። ሕዝቡ ለዘመናት ተርቦ ተርቦ ተርቦ “መጥገብን” ሳይሆን “መመገብን” እንኳ የረሳ ስለሆነ መንግሥት በሚባለው በማንኛውም አካል ወይም ቡድን ላይ እምነት አጥቷል። ከአጼው ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚሾመው ሁሉ “ችግርህን አቃልልሃለሁና ምረጠኝ” እየተባለ፣ ግን ደግሞ ባንዳቸውም የግዛት ዘመን ቤተሰቡን መመገብ ያልቻለውን ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያን አርሶ አደር ሕዝብ፣ የዛሬዎቹ የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን በምን ተዓምር ባጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡለት እንደሚችሉ አልታይህ ያለኝ ጉዳይ ነው። ሕዝቡ ዛሬ እየተራበ ነው፣ ረሃብ ደግሞ ቀጠሮ አይሰጥም። “ከሃያ ወያም ሰላሳ ዓመት በኋላ ኤኮኖሚያችን አድጎ ምግብ በሽበሽ ይሆናልና እስከዚያ ድረስ ግን እየተራብክም ቢሆን ታገሰኝ” ቢሉትም የመታገስ ዓቅም ያለው አይመስለኝም። ቄሮና ፋኖም ከሃያ ወያም ሰላሳ ዓመት በኋላ ያገራችን ኤኮኖሚ አድጎ በሙያህ ሥራ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከሥራም ሥራ ታማርጣለህ ተብሎ ቃል የሚገባለት ትውልድ አይደለም። ኑሮን ዛሬ መኖር ይፈልጋልና!

ስለዚህ ወገኖቼ – ፖሊቲከኞችና የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ሥልጣን ለመያዝ የምታደርጉት መሯሯጥ ተገቢ ቢሆንም፣ ሥልጣን ከያዛችሁ በኋላ ይህንን ለዘመናት የተከማቸና ፋታ የማይሰጠውን አገራዊ ችግር እንዴት አድርጋችሁ ለመፍታት እንደምትችሉ አሁን ዛሬ ከምርጫው በፊት ለኛ “ለምንመርጣችሁ” ዜጎች አንድ ሁለት ብላችሁ መርሃ ግብራችሁን በዝርዝር ብትነግሩን ጥሩ ይመስለኛል። “ተባብረው ምን ያረጉት ምን አይሆንም ነው የሚባለው”? በውነት ስለእውነት፣ እንወክለዋለን የምትሉትን ሕዝብ የምትወዱ ከሆነ በያላችሁበት እነዚህን ከብዙዎቹ በጥቂቱ ከላይ ያነሳኋቸውን ብሄራዊ ችግሮች እንዴት እንደምትቀርፉ ዕቅዳችሁን አካፍሉን፣ አወያዩን። በግልጽ ከመወያየት የተሻለ መፍትሔ የለምና! አለበለዚያ የፖሊቲካ ሥልጣን በጨበጣችሁ በማግሥቱ፣ የተራበው ሰፊ ሕዝብና ባዲስ አበባ ዙሪያ በተጠንቀቅ ቆሞ የሚጠባበቀው ቄሮ በሰላማዊ ሰልፍ ያጣድፋችኋል። እናንተም ቅጽበታዊ መፍትሄ ለማግኘት ስለማትችሉ፣ ያው እንደተለመደው ሕዝቡን “ታገሰን፣ ባዶ ካዚና ነው የተረከብነው” ብላችሁ ሁከቱን ለማርገብ ትሞክሩ ይሆናል።  የተራበው ሕዝብ ግን ውጤት ለማየት እንጂ የናንተን ዲስኩር ለመስማት ጊዜ ስለሌለው እምቢ ብሎ በዓመጹ ይቀጥላል፣ “ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን” በማለት ፖሊስ ታሰማራላችሁ፣ ፖሊስና ሕዝብ ይጋጫሉ፣ እንደተለመደው ሰላማዊው ሕዝብ ይጎዳል፣ ተቃውሞው ይሰፋል፣ የተቀመጣችሁበትን ይህን መከረኛ የአራት ኪሎ ወንበር ገና ሳትላመዱት፣ ተገድዳችሁ የምትለቁበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል። ሌላ የፖሊቲካ ቡድን ደግሞ ይተካችሁና ሌላ ዙር ዕውን የማይሆን ተስፋ ለሕዝቡ መስጠት ይጀምራል። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ! ለዘመናት የኖርነውና የሰለቸን የማማ በሰማይ ባዶ ሕይወት እንደገና መጀመር!

ይህ እንዳይሆን እንግዲህ ወገኖቼ፣ ካሁኑ የሚጠብቃችሁን የችግሮችን ክምር በውል ተገንዝባችሁ አቅማችሁን እንድትገመግሙ አደራ እላለሁ። በኔ ግምት ብዙዎቻችሁ፣ “ዋናው ነገር ተወዳድሮ ማሸነፍ ነው እንጂ ሌላው ሁሉ ቀላል ነው” ብላችሁ የምታስቡ ይመስለኛል። ያንዳንዶቻችሁን የቀን ተቀን ስብከትና መርሃ ግብራችሁን ሳጤን፣ ዓላማችሁ በሥልጣን ወንበር ላይ ከመቆናጠጥ የዘለለ አይመስለኝም። ትልቅ ስህተት ነው! አዎ ባደጉ አገራት፣ የአበበም ሆነ የቶለሳ፣ የሓጎስም ሆነ የኤልቤሞ ፓርቲ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ ባገሪቷ ኤኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ኢምንት ነው። አገራችን ግን ከነዚያ ተርታ ስላልተመደበች ዋናው ችግራችን የአበበ ሆነ የቶለሳ፣ የኤልቤሞ ወይም የሓጎስ ፓርቲ ማሸነፍ ሳይሆን አሸናፊው አራት ኪሎ ከገባ በኋላ ይህንን ዘርፈ ብዙ የሆነ ብሔራዊ ችግራችንን እንዴት አድርጎ እንደሚቀርፍ ነው። ለዚህም ነው አንዳንዴ ሳስበው፣ እነዚህ የፖሊቲካ ድርጅቶች የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ወርድና ርዝመት በደንብ ባይገነዘቡት ነው እንጂ፣ ለምን ብለው ነው ራሳቸውን እዚህ ውስጥ የሚከቱት የምለው። ግን ደግሞ ሕይወት መቀጠል ስላለበት፣ እናንተ ከማህበረስቡ መሃል ንቁ የሆናችሁ ሰዎች ተሰባስባችሁ የፖሊቲካ ድርጅት በመፍጠር እንደ ዜጋ የፈለገውን መስዋዕት ለመክፈል መደራጀታችሁ እስየው ይሰኛል። መደራጀት ብቻ ግን በቂ አይደለም። ችግሮቹን ዛሬ ለመቅረፍ ሳይሆን በሂደት እንዴት አድርጋችሁ እንደምትቀርፉት የሚረዳና አስተማማኝ የሆነ የረጅሙን ጉዞ ፍኖተ ካርታ ካሁኑ ማዘጋጀት አለባችሁ። የችግሩ ግዝፈት ጎልቶ እየታየ፣ ከወዲሁ የመቅረፍያ ዘዴዎችንና ስልቶችን ደግሞ ከሕዝብ ጋር በግልጽ ሳትወያዩና መተማመን ሳይደረስበት ለፖሊቲካ ሥልጣን ወንበር ብቻ ኃይልን ማስተባበር ግን ትክክል አይመስለኝም፣ በታሪክ ፊትም ተጠያቂ ያደርጋችኋል።

ስለዚህ ወገኖቼ! እስቲ እቅዳችሁን አካፍሉንና በአደባባይ ተወያይተን አንዳች ዓይነት ውሳኔ ላይ እንድረስ። በጉጉት የሚጠብቀውም ሕዝባችን በተለይም የኔ ዓይነቱ አንጋፋ ትውልድ፣ በዕድሜ ዘመናችን የኤኮኖሚ ዕድገቱን ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ የማናይ መሆኑን ቁርጣችንን አውቀን፣ እየተራብንም ቢሆን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ቢያንስ ቢያንስ ልጆቻችን የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለብሩሁ ነገ ተባብረን በጋራ እንድንዘምት በጋራ እንወያይ። ውይይቱን ደግሞ ለማዘጋጀትም ሆነ ለመምራት ግዴታ ያለባችሁ እናንተ የፖሊቲካ ድርጅቶች ናችሁና ታሪካዊ ግዴታችሁን ተወጡ! ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛላችሁ።

*******

ጄኔቫ፣ ሃምሌ 19 ቀን 2018 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

Share: