“እኔ የተገነዘብኩት የፖለቲካን ችግር መፍታት የሚቻለው ከሽምግልና ይልቅ በፖሊሲና በህግ መሆኑን ነው” አትሌት ሀይሌ

አስቴር ኤልያስ

በሀገራችን ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚደርሱ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በመፍታት በኩል ሽምግልና ጉልህ ስፍራ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሽምግልና ከፍተኛ ስፍራ ይሰጣል፤ ሽምግልናን ረግጦ አይሄድም፡፡ዋናው ጉዳይ ማስታረቅና ማስማማት ስለሆነም በዚህም በዚያም ብሎ ያስታርቃል፤ ያስማማል፡፡ ‹በሽምግልና የተያዘ ጉዳይ ይውል ያድር ይሆናል እንጂ ፣ሳይሳካ የሚቀርበት ሁኔታም እምብዛም አይደለም፡፡

ለሽምግልና የሚፈለግ አንድ ሰው የግድ አዛውንት መሆን አይጠበቅበትም፤ ሽምግልና ጾታንም ሆነ ትምህርትን እንደ መስፈርት አይመለከትም፤አባቶች እንደሚሉት ለሽምግልና የሚታሰብ ሰው ምራቁን ዋጥ ያደረገ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በእርግጥ ይህ ለሽምግልና ብቻውን ብቁ ያደርገዋል ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ማመዛዘንና በሰዎችም ዘንድ ተቀባይነት ወይም አመኔታን ያተረፈ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሽምግልና የሚከበር እና ብዙ ችግሮች የሚፈቱበት ቢሆንም፣ ነገሮች አልጋ ባልጋ ላይሆኑለት ይችላሉ፡፡ በሽምግልና ወቅት ብዙ እንግልት፣ ስቃይና ውጣ ውረድ ሊያጋጥም እንደሚችል በውስጡ ያለፉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ የተያዘው ጉዳይም ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበትና ምናልባትም ዓመታትን አስቆጥሮም ሊሳካም ላይሳካም ይችላል፡፡ ሽምግልና በመሠረቱ በክፍያ የሚፈጸም አይደለም፡፡ከፍተኛ ዋጋ ቢከፈልበትም ዋጋ አይጠየቅበትም፡፡ለክፍያ የሚደረግ ድርድርም አይኖርም፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለሽምግልና የሚቀመጡ አካላት ውጤታማ ለመሆን ከምንም በላይ በጎ ህሊና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሚሸመግሏዋቸው መካከል ለማንኛቸውም ሊያደሉ አይገባም፤ በቀና መንፈስና በእውነት ላይ ተመስርተው የሚያደርጉት ሽምግልና ቀንቷቸው ጉዳዩ ሳይሳካ ቢቀር እንኳ ከህሊና እዳ ነጻ መሆን ይኖርባቸዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዳግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኙ አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሽማግሌዎች አንድን ችግር ተመልክተው ፈር እንዲይዝ ያደርጋሉ፤ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ መላ ይፈጥራሉ፤በኢትዮጵያ ሽምግልና ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ የመቅጣት ስልጣን ግን የለውም፡፡
የፖለቲካ ምሁሩ እንደሚሉት፤ ከዛሬ ሃያና ሠላሳ ዓመት በፊት የነበረው ሽምግልና እና የአሁኑ ሽምግልና በባህሪው ይለያያል፡፡ ፈተና የሚሆኑ ችግሮችም የዚያኑ ያህል ልዩነት አላቸው፡፡ የሽምግልናው ባህሪ የተቀያየረበት ምክንያት ቀደም ሲል ሽምግልና ወይም ማስታረቅ የሞራል ልዕልና ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት መንፈሳዊም ሆነ ባህላዊ ይዘት አለው ማለት ነው፡፡ ሽምግልናውን ከምንም ነገር ጋር በተለይ ከገንዘብና ከጥቅማጥቅም ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በተለይ ግሎባላይዜሽን በሽምግልናውም ሆነ በባህል ላይ ተጽዕኖ እያሰረፈ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣በዚህ የተነሳም ሽምግልና የንግድ አካሄድ እየተላበሰ መምጣቱን አቶ አበበ ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በሽምግልናው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያርፍ ያደርጋል፡፡
‹‹በድሮ ጊዜ ሽማግሌ ፍጹም ትክክለኛ ነገር ይዞ ነው የሚጓዘው ተብሎ ይታሰባል፡፡ የሞራል ልዕልናም አለ፡፡ለሚሰራውም ጥንቃቄ ይወሰዳል፤ለትውልድም ይታሰባል፡፡በአሁኑ ወቅት ግን ግለሰባዊነት በዝቷል፡፡ መዋሸት፣ ማጭበርበርና በልጦ መገኘት እንደ አንድ አሸናፊነት እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተደማምረው የሽምግልናን ዋጋና ተዓማኒነት በተወሰነ መልኩ እየጎዱት ይገኛሉ ይላሉ ፡፡

እንደሚታወቀው፤ የባልና ሚስት፣ የቤተሰብ፣ ወዘተ ግጭት በሽምግልና ይያዛል፤ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ከመመልከቱ በፊት ሽማግሌዎች እንዲያዩት ያደርጋል፡፡ በግጦሽ መሬት ፣በውሃ፣ በወሰን ወዘተ.. ሳቢያ ግጭት ሲፈጠር ለመፍታትም እንዲሁ ሽምግልና ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ሽማግሌዎች አንተም ተው አንተም ተው ብለው አይነኬ የሚመስለውን ጉዳይ ሳይቀር ይፈቱታል፡፡
ሽምግልና ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችንም ለመፍታት ያገለግላል፡፡ በሀገራችን ከወሰን እና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች እየተቀሰቀሱ የሚገኙ ግጭቶችን በሽምግልና ለመፍታት ይሰራል፡፡መንግሥት የማረጋጋት ሥራ ካከናወነ በኋላ ችግሩን እና ዘላቂ መፍትሄውን ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች ፣ ወዘተ እንዲያፈላልጉ ይደረጋል፡፡

በሀገራችን በሽምግልና የተያዙ አንዳንድ ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ተሳክተው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በእንጥልጥል የሚቀሩበት፣ ሌሎች ደግሞ ቆይተውም የተሳኩበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከድንበር ጋር ተያይዞ ወደ 100 ሺ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ይህን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት ሁለቱ ሀገሮች የአልጀርስ ስምምነትን ቢፈራረሙም ድንበሩን ከማካለል ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ተግባራዊ ሳይደረግ ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወገኖች ታዲያ ሽምግልና ለመግባት ሞክረዋል፡፡በቅርቡ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የአገር ቤትና የአሜሪካ ሲኖዶሶችን ለማስታረቅም እንዲሁ ሽምግልና ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በአገሪቱ የሽምግልና ቡድን ውስጥ በመሳተፍ ከአስር ዓመት በላይ ሰርቷል፡፡ሀይሌ እንደሚናገረው፤ እሱና የሽምግልና አጋሮቹ በመጀመሪያ ሰብሰብ ብለው የሽምግልና ቡድን ያቋቋሙት ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ማስፈታትን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ በዚህም እስረኞቹን ከመንግሥት ጋር በማግባባት ለማስፈታት ሰርተዋል፡፡
‹‹የምርጫ 97 ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ የሽምግልና ቡድኑም ብዙ ተፈትኗል›› በማለት አትሌት ሀይሌ ከ13 ዓመት በፊት የነበረውን ጊዜ እና የተከፈለውን ዋጋ ያስታውሳል፡፡ ለዚህ ሽምግልና በመንግሥት በኩል ተቋቋሙ የሚል ጥሪ እንዳልቀረበ፣በራሳቸው ተነሳሽነት የሽምግልና ቡድኑን ማቋቋማቸውን ያብራራል፡፡ ይህን ጉዳይ የያዙበት ምክንያት አንድና አንድ መሆኑን በመጥቀስም ጉዳዩ የአገር ጉዳይ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ አትሌት ሀይሌ እንደተናገረው፤የምርጫ 97 ጉዳይን ሳይቋጩ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይን በሽምግልና ለመያዝ ዝግጅት ማድረግ ተጀምሮ ነበር፡፡ይህም በእንጥልጥል ላይ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሲኖዶሶች የሽምግልና ጉዳይ ይጀመራል፡፡ እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ሌሎች የግለሰብ ጉዳዮች በሽምግልና ተይዘው ነበር፡፡

ከምርጫ 97 ጋር የተያያዘው የሽምግልና ጉዳይ ውጤታማ ሥራ የተከናወነበት መሆኑን የሚጠቅሰው አትሌት ሀይሌ፣ በወቅቱ እነ ፓስተር ዳንኤል፣ ፓስተር በቀለና ሌሎችም በሽምግልናው ቡድን ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ አትሌት ኃይሌ እንደሚለው፤ የምርጫ 97 ጉዳይ በሽምግልና እንዲታይ ለማድረግ ከፍተኛ ምልልስ አጋጥሟል፡፡እስር ቤት መመላለስ እንዲሁም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር መወያየት ዋና ሥራ ነበር፡፡ አቶ መለስ ከሚመሯቸው ኮሚቴዎችጋር መወያየትም ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
‹‹አንዱ የራሱ ሐሳብ እንዲሰማ ይፈልጋል፤ሌላው ደግሞ ‹‹እንዴት ሆኖ›› ይላል፡፡ ይህ ጉዳይ ሽምግልና ትልቅ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን ያመለከተ ክስተት ነበር.. ሲል ያብራራል፡፡
‹‹በመሰረቱ የፖለቲካን ችግር በሽምግልና መፍታት ፈታኝ ነው፡፡ እኔ የተገነዘብኩት የፖለቲካን ችግር መፍታት የሚቻለው ከሽምግልና ይልቅ በፖሊሲና በህግ መሆኑን ነው››የሚለው አትሌት ሀይሌ፣ ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም ውጤቱ ማማሩን ግን ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያና ኤርትራን ጉዳይ ለመሸምገል ከ11 ዓመት በፊት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከሽምግልናው ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች ቢሰሩም ምንም አይነት ውጤት እንዳልተገኘ ይገልጻል፡፡ አትሌት ሀይሌ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ተይዞ በነበረው ሽምግልና እንደ ምርጫ 97 የጎላ ሚና አልነበረንም ይላል፡፤እንዲያም ሆኖ ግን በዚህ ጉዳይ ላይም ሽምግልናው ስኬታማ ይሆን ዘንድ የማመቻቸቱን ሥራ በትጋት ተወጥተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ በኩል ብዙ ሰርተን ነበር፡፡ ትልቁ ችግር የነበረው በኤርትራ በኩል በቂ ሽማግሌዎች ባለመኖራቸው ነው›› ያለው አትሌት ሀይሌ፣ይህ ስራም በመላላክ ይሰራ እንደነበር ይገልጻል፡፡‹‹በሽምግልናው ውስጥ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ደብዳቤዎችን በመላክ ያገኟቸው ነበር፡፡ በወቅቱም ከኤርትራ መንግስት ሲሰጣቸው የነበረው ምላሽ ‹‹የአልጀርሱ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ይተግበር›› የሚል ነበር›› ሲል ይብራራል፡፡
‹‹በኛም በኩል ጉዳዩ እንዲፈታ እንፈልጋለን፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት ከመጀመሪያው አንስቶ በመርህ ደረጃ ተቀብለናል፡፡ በዝርዝር ስንመጣ ግን የድንበሩ ጉዳይ ለሁለት የሚከፍል በመሆኑ እንነጋር የሚል ሐሳብ በወቅቱ ነበር ፡፡ ይሁንና ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ሲንከባለል ቆይቶ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እርምጃ መፍትሄ አግኝቷል፡፡››ሲል ይጠቁማል፡፡
ሁለቱም አገሮች ሲጀመርም ይግባኝ የሌለው ጥያቄ ማቅረባቸውን ፣ሊደረግ የነበረውም ውሳኔውን እንዲቀበሉ መሆኑን የጠቀሰው አትሌት ሀይሌ፣ሁለቱም ውሳኔውን መቀበላቸውን፣ ችግሩ አፈጻጸም ላይ እንደነበረም ያብራራል፡፡ ጉዳዩ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲንከባለል የቆየው በዚሁ ምክንያት ነው ይላል፡፡
‹‹በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጉዳይ እኛ 11 ዓመት ሙሉ እንሂድበት እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአንዴ ፈር አስይዘውታል ሲል ይገልጻል፡፡ በእርግጥም ደግሞ በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩን አካሄድ የተገኘውን ውጤት ሳስተዋል እኛ ምንም አልሰራንም ማለት ይቻላል›› ሲል ይገልጻል፡፡፡

አትሌት ሀይሌ በወቅቱ የጀመሩትን የኢትዮ ኤርትራ ሽምግልና ጉዳይ ሲያስተውስ የቀድሞው የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ትዝ ይሉታል፡፤ እሳቸውም ‹አንተ ለምንድን ነው ከዚህ ሁሉ ጣጣ ድንበር ላይ ከኤርትራዊው ዘረሰናይ ጋር የማትሮጠው‹ ብለውት እንደነበር ያስታውሳል፡፡እሱም በወቅቱ ፈቃደኛ መሆኑን ለአምባሳደሩ ገልጾላቸው እንደነበርና ጉዳዩ ትንሽ ወስብስብ ሆኖ ሩጫው ሳይካሄድ መቅረቱን ይናገራል፡፡ በአሁኑ ውጤት ላይ የእነርሱ እጅ ወይም ሽምግልና እንደሌለበት የተናገረው አትሌት ኃይሌ፣ ይህንን ታሪክ የሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ሽማግሌዎቹም በተከናወነው ተግባርና በተገኘው ውጤት መደነቃቸውን ያብራራል፡፡

አትሌት ሀይሌ እንዳለው፤በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ጉዳይ ሽማግሌዎች ለረጅም ጊዜ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ጉዳዩም ለ11 ዓመታት ያህል ተይዞ ነበር፡፡ይሁንና በእነዚህ ዓመታት ጉዳይ ይሄድ ይሄድና የሆነ ቦታ ሲደርስ ሲቆም አለያም ወደኋላ ሲመለስ ቆይቷል፡፡ የሽምግልናውን ዋና ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩት የአሁኑ ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ነበሩ ማለት ይቻላል ያለው አትሌት ሀይሌ፣አቡነ ማትያስ ውጭ በነበሩ ጊዜ ከፍተኛ ተግባር ማከናወናቸውን ይገልጻል፡፡ ሁለቱን ሲኖዶሶች በማቀራረብ ቀጥሎም በማዋሀድ በኩል ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥሎ ፓትርያርኩ በዚህ እርቅ ላይ ትልቁን እውቅና መውሰድ አለባቸው የሚል እምነት እንዳለው አትሌት ሀይሌ ይናገራል፡፡ ፓትርያርኩ ከመጀመሪያው አንስቶ ጉዳዩ ወደ ስምምነት እንዲመጣ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ሁሌም ወንድሞቻችን ወደ አገራቸው ይግቡልን፤ችግር ካለም እንነጋገር ይሉ ነበር ሲል ይገልጻል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዶክተር አብይ ጉዳዩን እንደያዙ ሁሉም በአንድ አፍታ መስመር መያዝ ቻለ፡፡አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዳዩን አሳኩ ማለት ይቻላል፡፡›› ያለው አትሌት ሀይሌ፣ የሽምግልና ቡድኑ በሲኖዶሱ ዙሪያ የማመቻቸት እንጂ የሽምግልና ሥራ እንዳልሰራ ይገልጻል፡፡‹‹እኛ የያዝነው ማመቻቸት እንጂ ሽምግልና ነበር ለማለት ይከብደኛል›› በማለትም ስራውን በአስገራሚ ሁኔታ ፍጻሜ ላይ እንዲደርስ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ‹‹እኛ በምርጫ 97 ወቅት በሽምግልና ሰርተናል፤በዚህ በሲኖዶሱ ጉዳይ ግን ለማመቻቸት ነው ስንጥር የቆየነው፡፡ በኤርትራም ጉዳይ ሁለቱ አገሮች እንዲገኛኙ እንዲሁም ችግራቸውን በጋራ እንዲፈቱ ነው ተንቀሳቅሰን የነበረው›› ሲልም ይገልጻል፡፡
እርሱ እንደሚለው፤ የሲኖዶሶቹም ጉዳይ እንዲሁ የቤተ ክርስትያኒቱ ህግና ቀኖና አለ፤ ያንን ቀኖና ተከትለው ሲያስፈጽሙ የነበሩት የኃይማኖት አባቶቹ ናቸው፡፡ እነሱ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል ፡፡‹እኛ ይህን ጉዳይ ልንሸመግል አንችልም ፡፡ ምክንያቱም ልጅ አባትን ማስታረቅ ይከብደዋል፡፡ ‹‹ኃይሌ ማለት የሶኖዶሶቹን ጉዳይ ሲያመቻቹ ከነበሩት መካከል አንዱ ነው እንጂ አሸማጋይ አልነበረም፡፡ በጥቅሉ ዕድሜ ለዶክተር አብይ የረጅም ጊዜ ምኞታችን እውን ሆኗል›› ሲል ገልጿል፡፡

አትሌት ኃይሌ ፣ አሁን እየታየ ያለው ለውጥ መልካም ሆኖ ሳለ በአገሪቱ ውስጥ አንዳንድ ቦታ እያታየ ያለው አለመግባባት መፈታት እንዳለበትም ይጠቁማል፤‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ተደርጎ በሁለቱም ወገን ብዙ ሰዎች ተሰውተውበታል፤ ጦርነት ያስከተለብን ምንድን ነበር ? አሁን ሠላምንና አንድነትን ስንፈጥር ያገኘነው ጥቅም ምንድን ነው ? የሚለውን በማየት ማመዛዘን አለብን፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን በሁለቱም በኩል ተጠቂዎች ነን፡፡ ጦርነትን አሳምረን ለዘመናት አይተናል፡፡ ሀብት ብቻ ሳይሆን መስዋዕትነትም ከፍለናል፡፡ በጦርነት ሁሉንም ነገር እናጣለን፡፡ በሠላም ግን ሁሉንም እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በተለያየ ቦታ ብልጭ እያለ የሚገኘው ግጭት ማንንም አይጠቅምም፤ ጉዳዩን የሚያባብስና ዓላማ ያለው ሰው ቢኖር ራሱ ለአንድና ለሁለት ቀን ይጠቀም ይሆናል እንጂ ከሦስትና አራት ቀን በኋላ ከባድ ጸጸት ነው የሚሆንበት፡፡ አሁን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ግለሰቦች የራሳቸውን አጀንዳ ለማራማድ የሚያካሂዷቸው ናቸው ›› ይላል፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ እየታየ ያለው በጌድኦ እና በጎጂ መካከል የተከሰተ ክስተት ማንንም አካል አይጠቀምም፡፡ ‹‹አጋጣሚ ሆኖ አካባቢውንም አውቃለሁ›› የሚለው ኃይሌ፣ ‹‹ሁለቱም ብሄሮች ተጋብተውና ተዋልደው በመኖራቸው አንዱን በአንዱ ውስጥ ነው የምናገኘው›› ሲልም ያብራራል፡፡ እንደ እርሱ አባባል፤ እነዚህ ሁለቱ ብሄሮች በመካከላቸው አለመግባባት የተፈጠረበት ምክንያት የኢኮኖሚ ጉዳይ ሆኖ ከሆነም አንዱ ለሌላው ለቆለት ሠላምን ነው ማስፈን ያለባቸው፡፡ ያንን አስለቅቄ ይህንን እጠቀምበታሁ ሊባል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ አይሆንም፡፡ በመጨረሻ ውጤቱ ሁለቱንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ግጭት እርስ በእርስ ያጠፋፋል እንጂ ማንኛውንም ብሄር አይጠቅምም፡፡

ከዚህ ቀደም የሚገፋፉ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ በመሆን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ እየተፈላለጉና አገራቸውን እየናፈቁ ባሉበት በዚህ ወቅት እዚህ አገር ውስጥ ያለው ግን እርስ በእርስ መገፋፋቱ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ፍጻሜው ትዝብት ላይ የሚጥለን ይሆናል፡፡ አሁን ለውጡ ይህን አይነት አካሄድ የሚቀበል አይደለም፤ ለውጥንም እንዳለመፈለግ ይቆጠራል፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ መሬታችን 25 ሚሊዮን ህዝብ በነበርን ጊዜ ያለው መሬት ነው አሁንም ያለው፡፡ ተጠቃሚው ግን በየቀኑ እየጨመረ ነው የሚመጣውና ልማቱን በማፋጠን ሠላምን ለማምጣት መጣር የግድ ይላል›› ሲል ተናግሯል፡፡ በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ አስገራሚ ነው፡፡ በአንድ ቀን የመድረክ ንግግር የዘመናት ቁርሾ እየጠፋ ነው፡፡ለዓመታት በሽምግልና ሲሞከሩ የነበሩ ትልልቅ ጉዳዮች ወራት ባልሞሉ ጊዜያት ውስጥ እጅ ሲሰጡም ተስተውሏል፡፡ ከእነዚህ መካከል በዋናነት ሁለት ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህም አንደኛው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሞት አልባ ጦርነት ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የሁለቱንም ሀገሮች ዜጎች ሲያሰቃይ ኖሯል፡፡የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረጉት የሠላም ጥሪ እና ባገኙት ፈጣን ምላሽ ኢትዮጵያውያኑንና ኤርትራውያኑን ብቻ ሳይሆን የዓለም ማህበረሰብን ያስደመመ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡  በተመሳሳይ ምንም እንኳ ጉዳዩ በሌሎች አካላትም ተይዞ የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥረት ችግሩ በቅርቡ እልባት አግኝቶ የሃይማኖቱን ተከታዮች ብቻም ሳይሆን ፣ መላውን ኢትዮጵያዊ እና መንግሥትን ጭምር አግራሞት ውስጥ ከቷል፡፡ በእርግጥ ሰሞኑን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ መግባባትና መተባበር ትልቅ ስኬት መሆኑ ይታመናል፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ህልም የሚመስሉ ነገሮችን እውን በማድረግ እንዲጨበጡ ያስቻሏቸው የኢትዮ ኤርትራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሁለቱን ሲኖዶሶች እንዲሁም ለብዙ ዓመታት ሲገፋፉ የነበሩ ተፎካካሪም ተቀናቃኝም የፓርቲዎችን ጉዳይ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአብይ ሽምግልና የተገኘ አብይ እርቅ ማለትስ ይህ አይደለምን?

Editor’s Note: This article appeared first on Addis Zemen News Paper under the title “በአብይ ሽምግልና አብይ እርቅ”.

.

Share: