ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም 115 ሚሊዮን ፓውንድ የዕርዳታ ስምምነት ተፈራረሙ

መላኩ ኤሮሴ

(አዲስ ዘመን)፡- የኢፌዴሪ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና የዩናይትድ ኪንግደም የዓለም አቀፍ ልማት ተቋም ዋና ፀሐፊ ፔኒይ ሞርዳውንት ስምምነቱን ትናንት በሚኒስቴሩ አዳራሽ ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ ከዕርዳታው ውስጥ 35 ሚሊዮን ፓውንድ የሀገሪቱን የታክስ ሥርዓት ለማዘመን ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፤ 80 ሚሊዮን ፓወንድ ለኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ የውጭ ሀገራት ስደተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይውላል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፤ ዕርዳታው ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ያግዛል ብለዋል፡፡ ዕርዳታው ለ100ሺ ሰው የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደ ሚያስችል ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ከዚህም ውስጥ 30ሺ ከተለያዩ ሀገራት መጥተው በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን ገደማ የውጭ ሀገራት ስደተኞችን እያስጠለለች ነው፡፡

በአገሪቱ የታክስ ስርዓትን ለማዘመን መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን አያይዘው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደምም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ አሁን የተደረሰው የዕርዳታ ስምምነትም የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል፡፡ ዕርዳታው መንግሥት ውጤታማ የታክስ ስርዓትን በመዘርጋት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ተከታታይ ዕድገት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ተገቢውን ታክስ እንዲሰበስብ እገዛ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ፍትሐዊ የታክስ ስርዓትን ለመዘርጋት ከማስቻሉም ባሻገር የታክስ መሰረቱን ለማስፋት ይረዳል፡፡ የዩናይትድ ኪንግደም የዓለም አቀፍ ልማት ተቋም ዋና ፀሐፊ ፔኒይ ሞርዳውንት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መወያየታቸውን አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ቀደም በሠሯቸው ሥራዎች ባስመዘገቡት ስኬቶች እንደሚኮሩም አንስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ስኬት በቀጣይ ጊዜያትም ለማስቀጠል መንግሥታቸው እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ማርዲያት እንዳብራሩት፤ የታክስ ስርዓት ለማዘመን የሚደረገው ድጋፍ ሀገሪቱ ከም ታመነጨው ሀብት መሰብሰብ ያለባትን ገቢ መሰብሰብ እንድትችል ያደርጋል፡፡ ሀገሪቱ ገቢዋን በአግባቡ መሰብሰብ ከቻለች በትምህርት፣ በጤና እና መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ከፍተኛ መሻሻል ማስመዝገብ ትችላለች፡፡ በቀጣይም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

Share: